tg-me.com/orthodox1/13085
Last Update:
᳀ #ኤጲፋንያ ᳀
᯼͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͟͞ ͟͞ ͟͞ ͟͞ ̸͞͝ ͟͞᯼
ንወዌጥን እንከ በረድኤተ እግዚአብሔር ልዑል ፡ ወበጸሎተ እሙ ንጽሕት ድንግል ፡ ወበኃይለ ክቡር መስቀል ከመ ንጽሐፍ በእንተ ኤጲፋንያ ➨ ልዑል በሆነው በእግዚአብሔር ረድኤት : ንጽሕት ድንግል በሆነች እናቱ ጸሎት : በክቡር መስቀሉ ኃይልና አጋዥነት ስለ ኤጲፋንያ መጻፍ እንጀምራለን፤
በኦርቶዶክሳዊቷ ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ሳምንታዊ ወርኃዊና ዐመታዊ የበዓላት መታሰቢያዎች አሉ፤ እነዚህም በዓላት ያለፈ ፡ በዕለቱ የሆነና ሊመጣ በተስፋ የሚጠበቅ ነገር ጭምር የሚታሰቡበት ተዝካር፣ ሕዝቦችም ምሥጢሩን እያሰቡ በደስታ የሚውሉባቸው የክብር ቀናት ናቸው።
ምእመናንም የበዓላትን ቀን በመንፈሳዊ ደስታ መጠበቅና መዘከር ፡ ማግነንና ማክበር እንደሚገባ መመሪያ የሚሰጠን የሥርዓት መጽሐፋችን መጽሐፈ ዲድስቅልያ በሃያ ዘጠነኛው አንቀጽ እንዲህ ሲል ይጀምራል "ኦ ፍቁራኒሁ ለእግዚአብሔር ዕቀቡ እንከ ዕለተ በዓላት ➨ እግዚአብሔርን የምትወዱ ተወዳጆች ሆይ የበዓላትን ቀን ጠብቁ" ከዚህም ጋር በማያያዝ ከከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን ኤጲፋንያ የመከበሩን ምክንያትና እንዴት ባለ መንገድ ሊከበር እንደሚገባው ሲያስረዳ ተከታዩን ማብራሪያ አስቀምጧል
"በዓለ ኤጲፋንያ ዘቦቱ አስተርአየ እግዚአ ስብሐት ለመለኮቶ በውስተ ጥምቀቱ በኀበ ዮሐንስ በውስተ ፈለገ ዮርዳኖስ … ኤጲፋንያ የክብር ባለቤት ጌታ በዮሐንስ ዘንድ የተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ መለኮቱን ያሳየበት በዓል ነው! (ዲድስቅልያ አንቀጽ ፳፱ ቁጥር ፫)
በሕማማቱ ሰኞ በሦስት ሠዓት በሚነበበው ግብረ ሕማማትም ይኽንኑ የቅዱሳን ሐዋርያት የሥርዓት መጽሐፍ ዲድስቅልያ በሚያሰማን ክፍል "በመንፈሳዊ ደስታ የበዓላትን ቀን መጠበቅ መፈጸም እንደሚገባ" በሚል መነሻ የተቀመጠው ምንባብ ቁጥር ፭ ላይ ኤጲፋንያ የሚለው ጥምቀቱን ተክቶ የሚከበርበት ቀን ጭምር ተመልክቶ እንደተነገረ ቀጥታ በመውሰድ የሚከበርበትን ቀን በማውሳት ነገሩን እንደሚከተለው ያጸናልናል፦
"ከዚህም በኋላ (ከበዓለ ልደቱ በኋላ) በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ ፊት የመለኮት ክብር የገለጸበትን የጥምቀቱን የኤጲፋንያን በዓል አክብሩ፤ በዕብራውያን አቆጣጠር በዓሥረኛው ወር በሰባት ቀን ሲሆን በግብጻውያን አቆጣጠር (ቀመረ ዲሜጥሮስን መነሻ ያደረገ ሊሆን ይችላል) ግን ጥር ፲፩ ቀን ይኸውም ጦቢ ማለት ጥር ነው በአምስተኛው ወር አክብሩ "
ኤጲፋንያ ለሚለው የቃሉ ምንጭ የግሪኩ ኤፒፋንያ (ἐπιφάνεια) ሲሆን መገለጥ መታየት አስተርእዮ የሚለውን ይተካል መነሻው ፌንየን (φαίνειν) ተርእየ፣ ተገለጠ ታየ ማለት ነውና። ለጌታችን ሲነገር በሰው ልጆች ሥጋ መታየቱ ከትንሳኤው በኃላ መገለጡ እና ዳግመኛ ለፍርድ መምጣቱን እየተካ በልሳነ ጽርእ ቅዱስ መጽሐፍ ተገልጧል! ግሪኩ ለሰዎች መጠሪያ ስም (ስመ ተጸውዖ) እየሠጠ ወንዱን ኤጲፋንዮስ ሴቷን ኤጲፋንያ ይላል Epiphania or Epiphaneia ( Ἐπιφανεία) is the feminine form of the name Epiphanius ) ከዚህ አያይዞ አስተርእዮን ለመለኮት መገለጥ ለአምላክ መታየት ለይቶ ለመንገር ግሪኩ ቴኦፋኒ/ቴኦፋንያ (θεοφάνεια) የሚለውን በተጨማሪነት ይጠቀማል።
በብሉይና ሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍትም ኤጲፋንያ የሚለው ቃል በልሳነ ጽርእ (Koine Greek)ተደጋግሞ ከአምላክ መታየት ጋር ተያይዞ ተገልጧል።
በብሉይ በመጽሐፈ መቃብያን ካልዕ "በእጃቸው ከጠላቶቻቸው ጋር ጦርነት ፡ በልባቸው ከአምላካቸው ጋር ጸሎት ይዘው ጠላት ድል ሲነሱ በእግዚአብሔር የክብር መገለጥ መደሰታቸውን" ይናገራል። ይህን መገለጥ በግሪኩ ኤጲፋንያ ብሎታል። በሐዲስ ኪዳንም በሥጋ ልደት መገለጡን ከሞት በኋላ በትንሣኤው ኃይል መታየቱን ዳግም ለፍርድ መምጣቱንም ሳይቀር ኤጲፋንያ ይለዋል።
ኤጲፋንያ የሚለው ዛሬ ላይ በምዕራባውያኑ ኬልቄዶናውያን ዘንድ ኤፒፈኒ (Epiphany) በሚል ጥምቀትን ብቻ በሚገልጽ መንገድ ይቀመጥ እንጂ ቀደምት ክርስቲያኖች አስተርእዮ መገለጥ በሚለው ትርጉሙ የሦስት ክብረ በዓላትን ምሥጢር ይዘው የበዓሉን ጥንተ ነገር ይዘከሩ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ
፩】 የክርስቶስ ጥምቀት (the baptism of Jesus)
፪】 የሰብአ ሰገል ወደ ቤተልሔም ተጉዞ አምላክን ማየት (the visit of the Wise Men to Bethlehem)
፫】 የቃና ዘገሊላው ተአምር (the miracle at Cana)
ምሥራቃውያኑ ጽባሓውያን (orientals) እና መለካውያን (Melchites) ግን እስከ ጥምቀቱ ድረስ የታየባቸውን መገለጦች ሁሉ አስተርእዮ ኤጲፋንያ ይሉታል። ከነዚህም
የልደተ እግዚእን ክብረ በዓል (celebration of Christ’s birth)፣ በሰብኣ ሰገል ክብሩ መገለጡን (the adoration of the Wisemen)፣ የጌታችን በልጅነቱ መታየቱን ከዚኽም ውስጥ በስምንተኘሰ ቀን ግዝረቱ (His circumcision) እና በዐርባ ቀን ወደ መቅደስ መውጣቱ (presentation to the temple ) እንዲሁም በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ መጠመቁ (baptism by John in the Jordan) ዋናዋናዎቹ የበዓሉ ምክንያቶች ናቸው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት ደግሞ ኤጲፋንያእና አስተርእዮ አንድነት የሚታዩ ሆነው መነሻው ከሰሙነ ጥምቀቱ ጋር ተገናኝቶ ይነገራል። ከዓመት እስከ ዓመት ያለውን የቅዱሳንን ዜና ገድልና ተዝካረ በዓል ከነማብራሪያው በአጭር በአጭር ቃል የሚዘግበው መጽሐፈ ስንክሳርም ኤጲፋንያ ከምሥጢረ ሥላሴው መገለጥ ጋር ተያይዞ እንዲህ ተገልጧል
"በዓለ ኤጲፋንያ አስተርእዮቱ ለመለኮት እስመ ባቲ አስተርአየ ምሥጢረ ሥላሴሁ ቅድስት (ልዩ የሆነች የሦስትነቱን ምሥጢር ገልጦባታልና መለኮት የተገለጠበት በዓል ማለት ነው!) Ipiphany the appearance of the Godhead,” because on this day appeared the mystery of the Holy Trinity " (ስንክሳር ጥር ፲፩ ቁ ፪)
ስንክሳሩ ተጨማሪ ሐሳብ በማከልም ከሦስቱ አካላት የአንዱ አካል የቃል/የወልድ መውረድ መታየት መገለጥ የሚታሰብበት መሆኑን ይዘግባል
በዓለ ኤጲፋንያ ዘበትርጓሜሁ አስተርእዮቱ ለመድኃኒነ ⇨ የኤጲፋንያ በዓል ይኸውም መድኃኒታችን የተገለጠበት ⇨ Epiphany, which is, being interpreted, the “appearance of our Our Savior (Lord Jesus)” (ስንክሳር ጥር ፲ ቁ ፮)
መጽሐፈ ሐዊ በ፶፯ኛው ባህል ደግሞ "እምነገረ ቅዱስ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳሳት ዘእለ እስክንድርያ ዘይትነበብ በዕለተ ጥምቀት" ብሎ
«ኤጲፋንያ ዘውእቱ በዓለ አስተርእዮ በዓለ ጥምቀት ⇨ ኤጲፋንያ ይኸውም የአስተርእዮ በዓል ፣ የጥምቀት በዓል ነው» ይላል።
የቅዱሳን ሐዋርያት የሥርዓት መጽሐፍ የሆነው ሲኖዶስም ይህንኑ ሐሳብ ያጸናል
BY ኦርቶዶክስ ተዋህዶ - 🇴🇷🇹🇭🇴🇩🇴🇽 🇹🇪🇼🇦🇭🇩🇴
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 283
Share with your friend now:
tg-me.com/orthodox1/13085